የፍልውሃ አገልግሎት ድርጅት አመሰራረት በአጭሩ
የአዲስ አበባ ከተማ አቆራቆር እና የፍልውሃ ቁርኝት
ስለ አዲስ አበባ አቆራቆር ብዙ መረጃዎች ቢኖሩም ስለዚሁ ርዕስ የተለያዩ ጸሐፊዎች ያቀረቧቸው ዘገባዎች ተመሳሳይነትና ተደጋጋፊነት ይታይባቸዋል፡፡ ጊዜው ዕሩቅ ባለመሆኑም ዕውነተኛው ታሪክ ሊዛባ ባለመቻሉ ነው፡፡ የጥንት ነገሥታት የቅርቡ ዘመን ንጉሥ ሣህለ ሥላሴም ጭምር አዲስ አበባንና ዙሪያዋን ደጋግመው እንደ አረፉባት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሣህለ ሥላሴ ፊንፊኔ ላይ በመሰንበት ተጠምቀውና በፍልውሃው ተጠቅመው እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ እንጦጦ ከመዲናችን ጋር ኩታ ገጠም በአሁኑ ዘመንም አካልዋ መሆንዋ ሲታወቅ እነ ዘርዓ ያዕቆብ ጭምር እዚህቹ አምባ ላይ ግንብ ገንብተው ሠፍረው እንደነበር የታሪክ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ስለ አዲስ አበባ አቆራቆር የዳግማዊ ምኒልክ የጽሕፈት ሚኒስቴር ጸሐፊ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ በጻፉት አጤ ምኒልክ የሚል ርዕስ በአለው መጽሐፍ እንዲሁም ከቅርብ ዓመታት በፊት አዲስ አበባ ትናገር በሚል ርዕስ ታጀበ በየነ በአቀረቡት ጹሑፍ ስለ አዲስ አበባ አቆራቆር ስለ ዘመኑ አስተዳደር ብዙ ተንትነዋል፡፡ አዲስ አበባ የተቆረቆረችው በእነዚህና በሌሎች መረጃዎች መሠረት ሕዳር 17 ቀን 1878 ዓ.ም ላይ ነው፡፡
በዘመኑ ከአዲስ ዓለም ወደ እንጦጦ ቤተ መንግሥታቸውን አዛውረው የነበሩት ታላቁ አፄ ምኒልክና ታላቋ ሰው እቴጌ ጣይቱ አዲስ አበባን የፊንፊኔ አካባቢ አዘውትረው ይጎበኙ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በተለይ እቴጌ ጣይቱ የሸገርን አካባቢ ጠበል ለመጠመቅ ማለት ፍልውሃ ለመታጠብ ተወዳጅ ልምዳቸው እየሆነ በመሄዱ ከብርዳሙ አምባ ከእንጦጦ እዚህ ረባዳ ክልል ከትሞ መኖርን በመምረጣቸው ልዩ ልዩ የሀገራቸውን ግዛቶች ጎብኝተው የተመለሱትን አፄ ምኒልክን ቃል በማስገባት መዲናቸውን ከእንጦጦ ፊንፊኔ /ሸገር/ እንዲያዞሩ ውሳኔ ላይ ደረሱ፡፡
ከዚያም እቴጌይቱ ንጉሠ ነገሥቱና መኳንንት መሣፍንቱ ፍልውሃ ለመታጠብ በወረዱ ጊዜ ያርፉባቸው ከነበሩ ድንኳኖች ዙሪያ ለሕዝብ መሬት እንዲታደል ተወሰነና ጎጆዎች በዕቅድ መቀለስ ጀመሩ፡፡ እንጦጦ የነበረው የአብያተ-ክርስቲያናት ግንባታ ሳያቋርጥ የተለያዩ የልማት ዕቅዶች ተነድፈው አዲስ አበባ እየለማች ሄደች፡፡ በአንጻሩም ፍልውሃው ነገሥታቱ፣ መኳንንቱና መሳፍንቱ ብቻ ሳይሆኑ ሕዝቡም በብዛት እንዲያዘወትረው የመታጠቢያ ሥፍራዎች ዘመኑ በፈቀደውና በተሻሻለ ሁኔታ እንዲሠሩ ተወስኖ ሥራው ቀጠለ፡፡ ሕዝቡም ከዳር ሀገር አንስቶ አዲስ አበባ ድረስ በረጅም ጉዞ እየተመመ መምጣቱን ቀጠለ፡፡
ለፍልውሃና ለጠበል እዚህ የሚገባውን ሕዝብ የማስተናገድ ፈሊጥ በመገኘቱ ሕዝቡ በፍልውሃው ዙሪያ ቤትመሥራትና አገልግሎቶች መፍጠሩን ተያያዘው፡፡በኢትዮጵያ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የፍልውኃ ምንጮች፣በተለያዩ ክልሎቿ እንደሚገኙ የተረጋገጠ ነው፡፡ ከመካከለኛው ምሥራቅ ከሊባኖስ አካባቢ በሚነሳው ታላቁ ስምጥ ሸለቆ ወሽመጥ ላይ ስለምትውል አብዛኛው መልክአ ምድራዊ አካልዋ የፍልውሃ የልዩ ልዩ ጠበሎች የተለያዩ ፍቱን መድኃኒት ያቋቱና ያዘሉ ንጥረ ነገሮች ምንጮች በቃላት ሊገለጹ የማይችሉ ፀጋዎችና አስደናቂ ተፈጥሮአዊ ገጽታዎች እንዳሏት የታወቀ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ፍልውሃም ከእነዚሁ ሕሩይና ግሩም በረከቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ህብረተሰቡ ለተለያዩ በሽታዎች ማለትም ለመገጣጠሚያ ብግነት፣ ለቁርጥማት፣ ለነርቭ በሽታ፣ ለአጥንት መሣሣት፣ ለጡንቻ መተሳሰርና መሰል የጤና ችግሮች ፈውስ ሰጪ የሆነውን ከከርሰምድር የሚፈልቅ የፍልውሃ ጠበል ተጠቃሚ ይሆን ዘንድ አፄ ኃይለስላሴ በዘመናዊ መልክ የፍልውሃ አገልግሎት ድርጅትን እንዲመሰረት አደረጉ፡፡